‹‹ሕጻናትና የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከማይደርሱበት ስፍራ የሚቀመጥ››

0
303

‹‹ሕጻናትና የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከማይደርሱበት ስፍራ የሚቀመጥ››  | አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ

ዶናልድ ትራምፕን ሳስብ በከፊል ትዝ የምትለኝ አንዲት ቁምነገር አዘል ቀልድ አለች፡፡
‹‹በተማሪነት ዘመናቸው የላቀ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች በስተመጨረሻ ዶክተር፣ ኢንጂነር፣ ፓይለት፣ ሳይንቲስት እና በመሳሰሉት ዘርፍ ሲሰማሩ ሰነፎቹ ደግሞ ፖለቲከኞች ሆነው ከላይ የተዘረዘሩትን የሚመሩ ይሆናሉ፡፡››

ዶናልድ ትራምፕ ግን ይሄንን ቀልድ ማሳካት ቢችሉም ዶክተርና ሳይንቲስቱን እየመሯቸው ሳይሆን እያደናገሯቸው ነው፡፡
ለምሳሌ ያህል ከተወሰኑ ሳምንታት በፊት HYDROXYCHLOROQUINE እና AZITHROMYCIN የተባሉ መድሃኒቶች ለኮሮና ታማሚዎች በአንድ ላይ ሲሰጡ ፍቱን (game changers) መሆናቸው ስለታወቀ በአስቸኳይ ጥቅም ላይ መዋል አለባቸው›› የሚል ትዕዛዝ አስተላልፈው ነበር፡፡ ትዕዛዙን የሰጡት ደግሞ በፌስቡክ ገጻቸውን ጭምር ስለነበር ይሄ መረጃ የደረሳቸው የሌላ አገር ዜጎች እኒህን መድሃኒቶች ገዝተው ያለባለሙያ ምክር በመጠቀማቸው ለሞት መዳረጋቸውን ሰምተናል፡፡

በቅርቡ ደግሞ በጭንቅላታቸው ያሰቡትን ሁሉ በግልጽ መናገር የሚወዱት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በእጃችን ላይ ያለ ቫይረስ ወደ መተንፈሻ አካላችን እንዳይተላለፍ የምናጸዳበት ሳኒታይዘር ለኮሮና ታማሚዎች በመርፌ ለምን አይሰጣቸውም?›› የሚል ምክረ-ሐሳብ መስጠታቸው ሚዲያዎችንና የሕክምና ሳይንቲስቶችን የሚያነጋግር ሆኗል፡፡

እንደውም በዚህ የትራምፕ ንግግር የተገረሙ አንድ ዶክተር ‹‹አስቸጋሪው ነገር ሕመሙን ከታማሚው ነጥሎ መምታት አለመቻሉ እንጂ ከሳኒታይዘር ይልቅ ኒውክሊየር ኮሮናን የማጥፋት ከፍተኛ ሃይል አለው!›› በማለት መልሰዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ግን አፋቸውን እንጂ ጆሯቸውን የማይጠቀሙ በመሆናቸው ‹‹ይሄን ብናገር ምን እባላለሁ›› ለሚለው ነገር ሳይጨነቁ ያሰቡትን ሁሉ እየተነፈሱት ነው፡፡

ምንም እንኳን በዚህ ዘመን፣ እንኳን እንደሳቸው ያለ የታላቅ አገር መሪ፣ ሌላውም ቢሆን የሚያስበውና የሚናገረው ነገር አንድ አለመሆኑ ይታወቃል፡፡ ማለትም የምናስበውን ሁሉ አንናገረውም፡፡

እንደውም በዚህ ጉዳይ ላይ ሳስብ ሶስት ዓይነት ሐሳቦች ያሉን ይመስለኛል፡፡ የምናስበው፣ የምናወራው እና የምንተገብረው
የምናስበው ሐሳብ እጅግ በጣም ብዙ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ከማንነታችን ጋር የማይሄዱ ተራ ሐሳቦችን ልናስብ እንችላለን፡፡

ቅዱስ ቦታ ተቀምጠን እርኩስ ሐሳብ፣ ከትልቅቅ ሰዎች ተርታ ተሰልፈን ትንንሽ ሐሳቦችን ስናስብ እራሳችንን እናገኘው ይሆናል፡፡ በዐይናችን የምናየው ነገር ሁሉ ወደ ጭንቅላታችን ሲደርስ ለሌላው ቀርቶ ለእራሳችን በሚያስጠላ መልኩ የሚተነተንበት አጋጣሚ አለ፡፡ ግን አንደበትን መቆጣጠር ጭንቅላትን እንደማፈን ከባድ ባለመሆኑ ያሰብነውን ትተን ማለት ያለብንን በመናገር እራሳችንን እናስከብራለን፡፡ካሰብናቸው ሐሳቦች መሃከል ለአድማጭንም ሆነ ለእራሳችን ክብር የሚመጥኑትን መርጠን እናወራለን፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ የምናስበውን ሁሉ እንደማናወራው ሁሉ፣ የምናወራውን ሁሉ አንተገብረውም፡፡ ይሄንንም ለማስረዳት መልካምነት ብንወስድ ዓለማውያኑ ይቅርና መንፈሳዊ የሚባሉ አባቶችም የሚሰብኩትን ሁሉ አይተገብሩትም፡፡ አሥርቱን ትዕዛዛት እየስተማሩ የሚተገብሩት ግን አምሥቱን ሊሆን ይችላል፡፡

ከዚህ አንጻር ‹‹እብድና ጤነኛ ሰው የሚለያየው ከጭንቅላት በተጨማሪ በአንደበትም ነው›› ማለት ይቻላል፡፡ የአዕምሮ ጤና ያለባቸው ሰዎች አንደበታቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው የሚያስቡትን ሁሉ ሲያወሩ፣ ጤነኞቹ ግን አንደበታቸውን በመግዛት ማለት ያለባቸውን ብቻ ይተነፍሳሉ፡፡

ከጤነኛው መሃከል ደግሞ ‹‹ማለት ያለባቸውን›› ትተው ‹‹መባል ያለበትን›› የሚናገሩት ፖለቲከኛ የሚል ስያሜ ይሰጣቸዋል፡፡ በመሆኑም አብዛኛው ፖለቲከኛ የሚታወቀው ‹‹እራሱ የሚያስበውን ትቶ ሕዝቡ የሚፈልገውን በመነገርና ጥቂቲን በመተግበር ነው›› ማለት ይቻላል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ግን ከእነዚህ ፖለቲከኞች የተለዩ ናቸው፡፡ እንደ ጭንቅላታቸው ሁሉ ለአንደበታቸውም ሙሉ ነጻነት ሰጥተው ያሰቡትን ሁሉ በማውራት ዓለምን እያነጋገሩ ነው፡፡ ‹‹ጭንቅላቴ ጫካ አይደለምና የምደብቀው የለም›› በሚል ፍልስፍና በአንደበታቸውም ሆነ በአካውንታቸው ያሰቡትን እንደ ወረደ ዘጭ በማድረግ የሚታወቁ ሆነዋል፡፡

እናም ዛሬ በወጣው መረጃ መሠረት ፕሬዝዳንቱ ድንክዬ ጣቶቻቸውን በሳኒታይዘር እያጸዱ ሳለ ብልጭ ያለላቸውን ሐሳብ እንደ ወረደ በመዘርገፍ ‹‹የኮሮናን ቫይረስ ሳኒታይዘር በመርፌ በመውጋት ለምን አናክመው?›› የሚል አስተያየት መስጠታቸውን የሰማው የዓለም የጤና ድርጅት የሳኒታይዘር ምርቶች ላይ እንዲህ የሚል ጽሑፍ እንዲጻፍ አዟል አሉ፡፡
‹‹ሕፃናትና ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከማይደርስበት ስፍራ የሚቀመጥ!››

እንደውም በዚህ የትራምፕ ንግግር የተገረሙ አንድ ዶክተር ‹‹አስቸጋሪው ነገር ሕመሙን ከታማሚው ነጥሎ መምታት አለመቻሉ እንጂ ከሳኒታይዘር ይልቅ ኒውክሊየር ኮሮናን የማጥፋት ከፍተኛ ሃይል አለው!›› በማለት መልሰዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ግን አፋቸውን እንጂ ጆሯቸውን የማይጠቀሙ በመሆናቸው ‹‹ይሄን ብናገር ምን እባላለሁ›› ለሚለው ነገር ሳይጨነቁ ያሰቡትን ሁሉ እየተነፈሱት ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here