በኮሮና ቫይረስ በሽታ ክስተት

0
261

በበሽታ ክስተት
የዓለም ኦሎምፒኩ፣ ኳሱ ቢቋረጥም
የስፖርት ትንታኔው
በስፖንሰር እገዛ- ቀጥሏል አሁንም
(አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ)

በሽታ የመከላከል አቅማችንን ለማጎልበት ጧት፣ ጧት ስፖርት መስራት ይመከራል፡፡ ግን ሬዲዮና ቴሌቪዥኑን ማለዳ ስትከፍተው የስፖርት ጋዜጠጮቻችን የተቋረጠውን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እየተነተኑ ታገኛቸዋለህ፡፡

ኮሮና በመከሰቱ የተነሳ ጃፓን ጠብ እርግፍ ስትልበት የከረመችው የዓለም ኦሎምፒክ፣ የጣሊያን ሴሪዓ፣ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ፣ የስፔን ላሊጋ፣ የኢትዮ ሊግ… እና የመሳሰሉት በመቋረጣቸው ባሁኑ ሰዓት አትሌቱም ሆነ እግር ኳስ ተጫዋቹ ስፖርት የሚሠራው ተጋጣሚውን ለማሸነፍ ሳይሆን ኮሮናን ለማሸነፍ ሆኗል፡፡

የእኛዎቹ ኤፍኤሞች ግን ‹‹ውድድሩ እንጂ ስፖንሰሩ አልተቋረጠም›› ብለው ጭምጭምታቸውን እያስጨመጨሙን ነው፡፡ በዚያን ሰሞን ሕዝባዊ እንቢተኝነት ተቀጣጥሎ ስንት ወጣት በየቀኑ በጥይት በሚረግፍበት ወቅት ‹‹ስለ አንድ የእግር ኳስ ተጫዋች ስብራት›› ሲያወሩን የነበሩት የሬዲዮ ጣቢያዎቻችንን አሁን ደግሞ ግጥሚያው በሌለበት ትንታኔውን አጧጡፈውታል፡፡

ታዲያ የሚገርመኝ ነገር ሚዲያዎቹ ብቻ ሳይሆኑ የሌለ ነገር እንዲተነትኑ፣ ኳሱ የሚጀመርበትን ማልዲኒ የሚያገግምበትን ቀን እንዲናገሩ ገንዘባቸውን የሚለግሱት ስፖንሰር አድራጊዎቹም ጭምር ናቸው፡፡

ይህ የሆነው ደግሞ የሚወራ ነገር ጠፍቶ ቢሆን ባላስገረመ ነበር! ሐቁ ግን አብዛኞቹ የሬዲዮ ጣቢያዎቻችንን በፍርሐት የተሸበቡ በመሆናቸው ባሕር ማዶ ተሸግረው የሌለውን ነገር ሲፈልጉ አጠገባቸው ያለውን ነገር የማየት ፍላጎቱ የላቸውም፡፡
ከሰሞኑን ለምሳሌ አንድ ግለሰብ 460,000 ካሜ (46 ሄክታር) መሬት አጥሮ መገኘቱን በመንግሥት ሚዲያዎች በኩል ተነግሮናል፡፡ ይሄም ሊሆን የቻለው መንግሥት ዜናው እንዲነገር ስለፈቀደ እንጂ በመንግሥት ሚዲያ ስር ያሉ የምርመራ ጋዜጠኞች አነፍንፈው መረጃውን ስለደረሱበት ሊሆን አይችልም፡፡

ግን ከመንግሥት ሚዲያዎች በፊት እንዲህ ያለውን የመሬት መቀራመት ሊነግሩን የሚገባቸው ገለልተኛ የሚባሉትና በአዲስ አበባ ዙሪያ ረዣዥም አንቴናዎቻቸውን የሰቀሉት የግል ሚዲያዎቻችን ነበሩ፡፡ እነሱ ግን ወዳጄ የዚህ አይነቱን ከባድ መረጃ ከመንግሥት ሚዲያዎች ላይ ተዘግቦ ካላገኙት በቀር በግል ምንጮቻቸው በኩል ሊደርሱበትም ሆነ ሊዘግቡት አይሹም፡፡

ታዲያ እኒህን ሚዲያዎች ሽባ ያደረጋቸው ፍርሐት ብቻ ሳይሆን ጥቅመኝነትም ጭምር ነው፡፡ ማለትም፣ አብዛኛውን ጊዜ ስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶች አገራዊ ችግሮቻችንን ለሚነቅሱ ሚዲያዎች ስፖንሰር ማድረግ መንግሥትን መተቸት ስለሚመስላቸው የገንዘብ ድጋፍ የሚያርጉለት ሚዲያ ለውጡን በአወንታዊ መልኩ የሚዘግብ ወይንም ደግሞ ፖለቲካውን ትቶ ኳሱንና ኪነ-ጥበቡን ብቻ የሚዘበዝብ እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡ ለዲሞክራሲ ግንባታ የራሳቸውን ሚና ከሚጫወቱ ሚዲያዎች ይልቅ በአዝናኝ ፕሮግራሞቻቸው እያዝናኑ አፈናን የሚያስቀጠሉ ፕሮግራችን ስፖንሰር ማድረግ ይመርጣሉ፡፡

ስለሆነም ምንም እንኳን አሁን ያለው የመናገር ነጻነት ያን ያህል አፋኝ ባይሆንም፣ ‹‹ስፖንሰሮቹ›› ሥልጣን ላይ ካለው መንግሥት ጋር ሲመሳሰሉ፣ ሚዲያዎቹ ደግሞ ስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶቻቸውን ይመስላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት መንግሥት ሙሉ ነጻነቱን ቢሠጣቸው እንኳን የራሳቸው ጥቅም አሳዳጅነት ነጻ እንዲሆኑ አያደርጋቸውም፡፡ (የአገር ውስጥ መረጃዎችን እየጎረጎሩ እንደ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጋዜጣ ስፖንሰር ከማጣት፣ እንደ አሃዱ ኤፍኤም በኦሮሚያ ፖሊስ ከመንገላታት ይልቅ ድንበርና ውቅያኖስ አቆራርጠው የውጩን ዓለም ውሎና አዳር በአማርኛ ቋንቋ እያወሩ የገንዘብ ምንጮቻቸውን ማስቀጠል ይፈልጋሉ፡፡)

ለምሳሌ ያህል አዲስ አበባ ላይ ሰፊ የሆነ የመሬት መቀራመትና ወረራ መኖሩን መንግሥት እራሱ የሚክደው አይደለም፡፡ ግን አዲስ አበባ ላይ የተሰቀሉት ረዣዥም አንቴናዎች በእንግሊዝ ስቴዲየሞች ውስጥ የሚደረጉትን ስፖርታዊ ውድድሮች እንጂ አዲስ አበባ ላይ ታጥረው የተቀመጡትን መሬቶች ማሳየት አይችሉም፡፡

በዚሁ ልክ ደግሞ የሌለው ነገር የሚያስጮሁ የዩቲዩብ ቻኖሎች አሉልህ! ቪዲዮቻቸው ላይ በጩኸት የተሞላ የፈጠራ ርዕስ ይለብዱና ውስጡን ስትከፍተው ግን ዘገባውን ቀርቶ ርዕሱንም ሳታገኘው ትቀራለህ፡፡ እናም የዩቲዩብ ቻናሎች ያልተሰራውን ፈጥረው ሲያወሩህ፣ የሜይን ስትሪም ሚዲያው ደግሞ የሚሠራውን ሁሉ ይነፍጉኻል፡፡

ስፖርቱን በተመለከተ ደግሞ በቤት ውስጥ ልንሠራቸው ስለሚገቡ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ግንዛቤ መፍጠር ሲችሉ የተቋረጠውን ውድድር የሚመለከት ትንታኔ በማለዳ ይዘው ይመጡና ‹‹አልጋህ ላይ ሆነህ አዳምጠን›› ይሉኻል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here